| በቤት ተሽከርካሪዎች ላይ ብቻ የሰሌዳ ቁጥር ማስተካከያ ሊደረግ ነው |
|
|
|
| Written by solomon | |||
| Thursday, 08 July 2010 16:18 | |||
|
የዲኤክስና ሚኒባስ ባለቤቶች ተቀናጅተው መሥራት ይችላሉ
የአዲስ አበባ ከተማ የቤት ተሽከርካሪዎች ቁጥራቸው 99 ሺሕ 999 ሊሞላ 500 ወይም 600 የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች ብቻ እንደሚቀሩ ሠራተኛው ገልፀው፤ እነዚህ ተሽከርካሪዎች ቀድሞ እንደነበረው ባለአምስት ዲጅት የሰሌዳ ቁጥር እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡ ማስተካከያ የሚደረግበት የቤት ተሽከርካሪዎች የሰሌዳ ቁጥር፤ ከቁጥሩ መጀመሪያ ወይም ከፊት ኤ፣ ቢ ወይም ሲ በመጻፍ የቁጥሮቹን ብዛት መጨመር መሆኑን ሠራተኛው ጠቅሰዋል፡፡ የእንግሊዝኛ ወይም የአረብኛ ፊደላትን ከፊት ለፊት በመጨመር በሚሊዮን የሚቆጠር ሰሌዳ ማምረት እንደሚቻል የተናገሩት የባለሥልጣኑ ሠራተኛ፤ ፊደሎቹ የሚቀመጡበት (ቅርፅ የሚወጣበት) ጥሬ ዕቃ ከውጭ ስለሚመጣ፣ ትዕዛዝ መሰጠቱንና እንደመጣም ሥራው እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡ ከመቶ ሺሕ በታች ያሉትን የሰሌዳ ቁጥሮች የሚያካትት ሰሌዳ ማዘጋጀት ያልተቻለበትን ምክንያት ሠራተኛው ሲገልጹ፤ ጥሬ ዕቃው የሚመጣው ከውጭ አገር ስለሆነ፤ ነባሮቹንም የሚያካትት የሰሌዳ ቁጥር ይዘጋጅ ቢባል፣ ወጭው ከባድ በመሆኑ በአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ ለጊዜው ችግር ሊፈጥር የተቃረበውን የአዲስ አበባ የቤት ተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ቁጥር ብቻ ለማስተካከል ውሳኔ ላይ መደረሱን አብራርተዋል፡፡ ለማስተካከያ የሚሆነው ጥሬ ዕቃ (ፊደሎቹ የሚቀረፁበት) የተለየ ቴክኖሎጂ የሚጠይቅ ባለመሆኑ፣ ወጪው በጣም ትንሽ ከመሆኑ አንፃር በነፃ የሚሠራ ያህል እንደሚቆጥሩት ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ ከ1935 ዓ.ም. (በወቅቱ የመሥሪያ ቤቱ ስም የተለያየ ነበር) እስከ 1973 ዓ.ም. ድረስ በብረት ላይ የሚታተም፣ ከ1973 እስከ 1994 ዓ.ም. አንፀባራቂ በሆነ ብረት ላይ የታተመ፤ ከ1994 እስካሁን ደግሞ የማይታዩ መለያዎችና የተለያዩ ፎርጅድ ቁጥሮች ለመሥራት የማይቻልባቸው፣ ለቤት መኪና፣ ለፖሊስ፣ ለታክሲ፣ ለኮር ዲፕሎማቶች፣ ለአፍሪካ ኅብረት፣ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ለዕርዳታ ድርጅቶች፣ ኢት የሚሉ በሁሉም መንገዶች መተላለፍ የሚችሉ፣ ተላላፊና የዕለት የሚሉ የሰሌዳ ቁጥሮችን ሲሰጥ መቆየቱን የባለሥልጣኑ ሠራተኛ አስታውሰዋል፡፡ በተያያዘ ዜና፣ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የአውቶሞቢል ተሽከርካሪ ምድብ ሥልጠና እና ፈተናን አስመልክቶ ለ38 አሠልጣኝ ድርጅቶች በፃፈው ደብዳቤ፣ ተገቢውን የማሠልጠኛ ተሽከርካሪዎችን በማዘጋጀት ከመስከረም 30 ቀን 2003 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማስጠንቀቁን ተከትሎ አለማማጆችና አሠልጣኝ ድርጅቶች ተቃውሞአቸውን እያሰሙ ነው፡፡ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በፃፈው ደብዳቤ፣ የአውቶሞቢል ካቴጐሪ (ምድብ) ለተግባር ሥልጠናም ሆነ ለፈተና የሚያስፈልገው የተሽከርካሪ ዓይነት፣ አሽከርካሪውን ጨምሮ 12 መቀመጫ ያለው ሚኒባስ እንደሆነ ቢገልፅም፤ "ሚኒባስ አውቶሞቢል አይደለም" በማለት በሥራው የተሰማሩት አብዛኛዎቹ ተቃውሞአቸውን ገልፀዋል፡፡ መስፈርቱ ትክክል እንዳልሆነ፣ በአውቶሞቢል ለመለማመድና በሚኒባስ ለመለማመድ የተመደበው ሰዓትም ሆነ ክፍያ አግባብነት የሌለው በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባው ይገልፃሉ፡፡ በሚኒባስና በአውቶሞቢል ሥልጠና የማሽከርከር ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ (መንጃ ፈቃድ) የሚያገኝ ሠልጣኝ፤ ሁለቱንም ተሽከርካሪዎች ማሽከርከር የሚችልበት አንድ ዓይነት መንጃ ፈቃድ ማግኘት ሲገባው፣ ለምን ለአውቶሞቢል ሌላ፣ ለሚኒባስ ሌላ እየተባለ ይከፋፈላል? በማለት የሚጠይቁት አለማማጅና አሠልጣኞቹ፤ የኅብረተሰቡን ፍላጐት ከመወሰንና መብት ከማሳጣት አኳያ ሊታይ እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡ የማለማመጃው ወይም የማሠልጠኛው ግቢ (ቃሊቲ የሚገኘው) በጣም ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ ለማሠልጠን አስቸጋሪ ከመሆኑም ሌላ፣ የግቢው ተቆጣጣሪዎች በተለማማጆቹና ባለማማጆቹ ላይ ያልተገባ ማመነጫጨቅና ሕገወጥ ተግባራት እየፈፀሙ ስለሆነ፣ የሚመለከተው አካል ክትትል በማድረግ ሁሉንም የማስተካከል ኃላፊነት እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡ በአዋጅ ወይም በሕግ የወጣው መመሪያ የተወሰኑ ባለሀብቶችን ለመጥቀም ታስቦ መሆኑን የሚገልፁት አለማማጆቹ፣ መንግሥት በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ከማበረታታትና ዜጐችን እኩል ከማየት ኃላፊነት ተነስቶ፤ ቤተሰቦቻቸውን ከመበተናቸው ወይም ለችግር ከማጋለጣቸው በፊት ሊታደጋቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ አሠልጣኞቹ እና አለማማጆቹ ያነሱትን ቅሬታ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የመንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን አንድ ኃላፊ፤ በዲኤክስ አንድ ሦስተኛውን፣ ቀሪውን በሚኒባስ አሠልጥነው 12 መቀመጫ ባለው ሚኒባስ ማስፈተን እንዳለባቸው የተገለጸው ከሦስት ዓመት በፊት መሆኑን በማስታወስ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ቢፒአርን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ ጀምሮ እንደተነገራቸው የገለጹት ኃላፊው፣ ዲኤክሱን ለመቀየር አቅም ከሌላቸው ሚኒባስ ካላቸው ጋር ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው፤ ካልሆነ ግን ሕጉን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር መመሪያው ተፈፃሚነት እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡ "የፍላጐት ማጣት እንጂ ያለመቻል አይደለም" ያሉት ኃላፊው፣ ከፊሎቹ ሙሉ በሙሉ ሚኒባስ ይሆናል ተብለን ለምን በዲኤክስ ሆነ ሲሉ፣ ከፊሎቹ ደግሞ ዲኤክስ ብቻ እንዲሆን የሚፈልጉ ቢኖሩም፣ በአገር ደረጃ ተግባራዊ ሳይሆን የቀረው የአዲስ አበባ ብቻ እንደሆነና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ከሰጠው የጊዜ ገደብ በኋላ ተግባራዊ እንደሚሆን አረጋግጠዋል፡፡ የተለያዩ ነገሮችን በማንሳት ነገሩን ለማጓተት ወይም ያልሆነ መልክ እንዲይዝ የሚንቀሳቀሱት ከ200 እንደማይበልጡ የተናገሩት ኃላፊው፤ ባለሥልጣኑ ዲኤክሶች ሙሉ በሙሉ ከሥራ ይውጡ አለማለቱንና አንድ ሦስተኛ (10 ሰዓታት) በዲኤክስ ቀሪው ሁለት ሦስተኛው (20 ሰዓታት) በሚኒባስ እንዲለማመዱ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡ በአዲሱ መመሪያ መሠረት፣ የአሽከርካሪነት ብቃት ማረጋገጫ ከድሮው በብዙ ነገር እንደሚለይ የገለፁት ኃላፊው፣ ቀደም ባሉት ጊዜ የሚሰጡት መንጃ ፈቃዶች በተሽከርካሪው ክብደት የተከፋፈሉ ሲሆኑ፣ የአሁኖቹ ግን በአገልግሎት ዓይነት መከፋፈላቸውን አሳውቀዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ዝም ብሎ በዘፈቀደ መመሪያ በማውጣት ብቻ መንጃ ፈቃዶችን መቀየር ፈልጐ አለመሆኑን፣ ከ150 አገሮች ተሞክሮ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊነቱ የተረጋገጠ መሆኑን በማጥናት መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፤ "እኛ ከዛሬ 40 ዓመታት በፊት ከእንግሊዝ በወሰድነው የመንጃ ፈቃድ ዓይነት ስንጓዝ፣ ዓለም ግን ብቃት ያለው አሽከርካሪ እንዴት ማፍራት አንደሚቻል በማሠልጠን ብቃት ያላቸውን አሽከርካሪዎች ማፍራት ከጀመረ ዘመናት ተቆጥረዋል" ብለዋል፡፡ ቀደም ብለው የመንጃ ፈቃድ ያወጡትን በተመለከተ፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መመሪያ እስከሚያወጣ ባለው መጠቀም የሚችሉ መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
|
|||
| Last Updated on Thursday, 08 July 2010 16:21 |
Add your comment
ADD
Comments, category: "amharic"
- የአዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጆች ሕትመቱን አቋርጠው ተሰወሩ (4)
- እኛ ካላሸነፍን ምርጫው መጭበርበሩ ይታወቃል ሲሉ የአንድነት አመራሮች አስታወቁ (2)
- አቶ ስዬ አብርሃ መንታ መንገድ ላይ መቆማቸው ታወቀ (1)
- ከአፄው ስርዓት ጋር የሚመሳሰል የምርጫ ቅስቀሳ በተምቤን ተጀመረ (1)
- ኢትዮጵያ ግብረ-ሰዶም ባለመፍቀዷና ግልገል ጊቤን በማልማቷ ሁማን ራይትስ ዎች ከሰሰ፤ አቶ ገብሩ አስራትና አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በምንጭነት ተጠቅሰዋል (1)
- የኢ/ጉ/ገ/ ባለሥልጣን 6 ህገ ወጥ ነጋዴዎች ወደ ህግ ማቅረቡን አስታወቀ (1)











