RedBlueDark SmallMediumLarge NarrowWideFluid
የዓባይ ተፋሰስ አምስቱ ፈራሚ አገሮች አንድነታቸው ተጠናክሯል PDF Print E-mail
Written by solomon   
Friday, 02 July 2010 06:52


ሱዳን
በአምስቱ አገሮች ላይ ጥያቄ አላት

  

የዓባይ (ናይል) ተፋሰስ አገሮች የውኃ ሀብት ሚኒስትሮች ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል አስራ ስምንተኛ መደበኛ ስብሰባቸውን አካሂደዋል፡፡ ይህ ስብሰባ በግብጽ ሻርም ኤል ሼክ ከተደረገው ልዩ ስብሰባ ተከትሎ የተካሄደ ሲሆን፣ ዋና አጀንዳ ተደርጎ የተያዘው የናይል ቤዚን ኢንሺኤቲቭ (Nile Basin Initiative) በጀትን ማጽደቅ ነበር፡፡

 


ሆኖም
ግን ከሚዲያ አካላት ትኩረት ተሰጥቶት የነበረው ጉዳይ የኢኒሺኤቲቩ ኮፕሬቲቭ ፍሬም ወርክ አግሪመንት (Cooperative Framework Agreement (CFA)) ላይ ነበር፡፡ ይህን ስምምነት ከዘጠኙ የኢንሺኤቲቩ አባል አገራት ውስጥ እስካሁን ድረስ አምስት አገሮች የፈረሙ ሲሆን፣ እነሱም ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ሩዋንዳ ናቸው፡፡ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ቡሩንዲ እና የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እስካሁን አልፈረሙም፡፡ በተለይ ግብጽ እና ሱዳን በስምምነቱ ሰነድ ውስጥ በውኃ ደኅንነት ላይ ባተኮረውና በአንቀፅ 14 ያልተስማሙ በመሆኑ፣ ተጨማሪ ውይይት እንዲደረግበት መጠየቃቸው የሚታወስ ነው፡፡

 

ስብሰባው ከታቀደለት ሰዓት አርፍዶ መጀመሩ ከነበሩት ታዳሚዎች ትንሽም ቢሆን ጥያቄዎችን አስነስቶ ነበር፡፡ የዓባይ ጉዳይ ለተፋሰሱ አገሮች አብይ ከመሆኑም በላይ፣ ሁሉም ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እያንዳንዱን ዕርምጃ እንደሚሔዱ የማይዘነጋ ነው፡፡ የስብሰባው አጠቃላይ ድባብ በአንድ ጎን ወንድማዊ ስሜት የተላበሰ ነበር፡፡ በተለይም የግብፁ የውኃ ሀብትና የመስኖ ሚኒስትር / መሐመድ ናስር ኤል ዲን አላም የኢትዮጵያ አቻቸውን አቶ አስፋው ዴንጋሞን መልካሙ ወንድሜ አስፋው (My good brother Asfaw) እያሉ በተደጋጋሚ ይጠሩዋቸው ነበር፡፡ በሌላው ጎን ደግሞ እያንዳንዱ አገር የጋራም ሆነ የግል ጥቅሙን ላለማስነካት ጥንቃቄ የተሞላበት መልዕክት ነበር የሚያስተላልፉት፡፡

 

"የግብፅ የሰባት ሺህ ዓመት ስልጣኔ መሠረት ያደረገው በአባይ ወንዝ ላይ ነው፡፡ ገበሬዎቻችን ምርቶቻቸውን የሚያገኙት ከአንዱ ዓባይ ወንዝ ነው፡፡ እኛ እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ወንዞች የሉንም፤" ብለው የተናገሩት / መሐመድ፣ ለሚያደርጉት እያንዳንዱ ውሳኔ እና ለሚፈርሙት እያንዳንዱ ሰነድ ጥንቃቄ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡ የሚዲያውን ትኩረት ስበው የነበሩት የግብፁ ሚኒስትር የዓባይ ጉዳይን በቀላሉ እንደማያዩ ነበር ሲገልጹ የነበረው፡፡ በዓባይ ውኃ ላይ ጥገኛ የሆኑ በርካታ ግብፃውያንን ውኃው በሌሎች አገሮች ስለሚፈለግ ቀዬአችሁን መልቀቅ አለባችሁ ብሎ ለሕዝባችን መናገር የእኛ ፍላጎት አይደለም ያሉት / መሐመድ፣ ግብፅ ዋነኛ የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነቷን ስለምታምን ከፍተኛ ድርሻ ማግኘት ስላለባት ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ይህ ማለት ግን ሌሎች የተፋሰሱ አገሮች በተሻለ አስተዳደር የውኃው ተጠቃሚዎች መሆን እንዳለባቸውም እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 

ግብፅ ለእህት አገሮችዋ የምታስተላልፈው መልዕክት በውኃው ላይ ጥገኛ የሆኑትን ሕዝቦችዋን ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ነው በማለት ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ከሱዳን በስተቀር የተፋሰሱ አባል አገሮች የግብፅ ጥያቄ የሌላውን አገር ጥቅም በማይጎዳ መልኩ መሆን አለበት ብለው ነበር በአንክሮ የገለጹት፡፡ ለዚህ አስተያየት ምላሽ የሰጡት የውኃ ሀብት ሚኒስትሩ አቶ አስፋው፤ በቪክቶርያ ሐይቅ እና በጣና ሐይቅ አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦችም ተመሳሳይ ጥያቄ ነው ያላቸው፤ እነሱም ውኃውን የመጠቀም መብት አላቸው ብለዋል፡፡   

 

የዶ/ መሐመድን ንግግር በመከተል፣ አቶ አስፋው ሲናገሩ፣ ምንም ያህል ኢትዮጵያ በርካታ ወንዞች ቢኖሯትም፣ ሁሉም የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የዓባይን ውኃ እኩል የመጠቀም መብት እንዳላቸው ገልፀዋል፡፡

 

"እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1929 የተደረገው ስምምነት ለሁለት አገሮች የድምፅን በድምፅ የመሻር መብት መስጠቱ ሚዛናዊ ያልሆነ በመሆኑ ነው አዲስ ስምምነት ያስፈለገው፤" ብለዋል አቶ አስፋው፡፡

 

ይህን ንግግራቸውን የሩዋንዳው አቻቸው አምባሳደር እስታኒሳልስ ካማንዚ በመጋራት፣ ኢኒሺኤቲቩ የተቋቋመበት ዋነኛው ዓላማ ለአባል አገሮች እኩል የሆነ ጥቅምና ይህንን ሀብት በደንብ መጠቀም እንዲያስችላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 

ባለፈው ግንቦት ወር በኢንቴቤ (ኡጋንዳ) በአራት አገሮች (ኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ዩጋንዳ) የተጀመረው ስምምነት፣ ከአሥር ዓመት በላይ የፈጀውን የተፋሰሱ አገሮችን እኩል የዓባይን ውኃ የመጠቀም የመጀመርያ ወሳኝ ዕርምጃ መሆኑ የማይዘነጋ ነው፡፡ አምስተኛዋ አገር ኬንያ በዚያው ወር ውስጥ በመፈረም ለስምምነቱ ተፈፃሚነት ያላትን ራዕይ አመላክታለች፡፡

 

ሌላው መሻሻል ያስፈለገው ስምምነት .. በግብፅ እና 1959 በሱዳን መካከል የተፈረመው ስምምነት ነው፡፡ ይህ ስምምነት ለግብፅ ሰማንያ አምስት በመቶ ውኃውን የመጠቀም መብት የሰጠ ሲሆን፣ የቀረውን አስራ አምስት በመቶ ለሱዳን ሰጥቷል፡፡ ይህ ስምምነት የተቀሩትን የተፋሰሱን አገሮች ችላ ያለ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ለዓባይ ወንዝ ሰማንያ አምስት በመቶ ውኃ እንደምትሰጥ የታወቀ ነው፡፡ አባል አገሮቹ የስምምነቱን ሰነድ ከፈረሙ በኋላ በየአገራቸው ፓርላማ እንዲፀድቅ ያቀርባሉ፡፡ ከፀደቀ በኋላም ሕግ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

የኢኒሼኤቲቩ ዋና ዳይሬክተር ሄንሪየት እንዶምቤ ሲናገሩ፣ ስምምነቱ ሲፀድቅ እያንዳንዱ አባል አገር ከታሪክ እና ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ በመፈረም፤ ነፃነቱ የማይገድብ መሆኑን በመረዳት እንዲያውም ላሉት ችግሮች መፍትሔ እንደሚሆን በማወቅ ይሁን ብለዋል፡፡

 

ይህን ስምምነት ለመፈረም እስከ ግንቦት 5 ቀን 2003 . ድረስ ጊዜ ያለ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ ነው ለመፅደቅ የሚቀርበው፡፡ ስምምነቱ ከፀደቀ በኋላ የዓባይ ተፋሰስ ኮሚሽን (Nile Basin Commission) መቋቋምን መንገድ ይጠርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

በንግግራቸው ወቅት / መሀመድ የኮሚሽኑን መቋቋም ግብፅ እና ሱዳን እንዲፋጠን ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ ከሌሎች አባል አገሮች የተሰጠው ምላሽ ጊዜው አሁን እንዳልሆነ እና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ስምምነቱ እንደሆነና ውድቅ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡

 

ከስብሰባው በኋላ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ግን አንድ ያልተጠበቀ አስተያየት በሱዳን የውኃ እና መስኖ ሚኒስትር በኢንጂነር ከማል አሊ መሐመድ ተሰጠ፡፡ አስተያየቱም አምስቱ አገሮች የፈረሙትን ስምምነት ወደኋላ አንመልሰውም በማለት፣ አቋማቸው የፀና መሆኑን በመግለፃቸው ነበር አስተያየቱን የሰጡት፡፡ "አምስቱ አገሮች ፈርመዋል፣ ይህ ደግሞ በጣም ወሳኝ የሆነ ሕጋዊ አንድምታ አለው፡፡ በተለይ የኢኒሺኤቲቩን የወደፊት እጣ ፈንታ እና ስምምነቱን በተመለከተ ነው፡፡ ሰነዱን በመፈረማቸው በአንድነት የመሥራትን ዓብይ መመርያ ጥሰዋል፤" ያሉት የሱዳኑ ሚኒስትር፣ እነዚህ ሕጋዊ አንድምታዎች እስከሚስተካከሉ ድረስ ሱዳን በኢኒሺኤቲቩ ያላትን እንቅስቃሴ ማቆሟን አክለው ገልፀዋል፡፡

 

ይህ አስተያየት በአዳራሹ ውስጥ የተገኙትን ተሳታፊዎች ያስገረመ ነበር፡፡ ይህ አስተያየት ያስቆጣቸው አቶ አስፋው፣ በአስተያየቱ ላይ ያላቸውን ምላሽ ሲሰጡ. "በመጀመርያ በውይይቱ ወቅት ይህንን እንቅስቃሴ ስለማቆም ጉዳይ የተወሰነ ነገር አልነበረም፡፡ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አይቆምም፡፡ ሱዳን እንደ አንድ አገር እንቅስቃሴ ማቆም ትችላለች፤ ግን ቢሆንም በዚህ ጉዳይ ላይ አልተወያየንበትም፤" ብለዋል፡፡ አቶ አስፋው ሲናገሩ አንዳንድ ማሳሰቢያዎች የተነሱ ነበሩ፡፡  እነዚህም በቃለ ጉባኤ ተይዘው ለቀጣይ ውይይት እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል፡፡

 

ሁሉም አባል አገሮች የራሳቸውን ጥቅም ላለማስነካት ጥንቃቄ እና ብልሃት በታከለበት ሁኔታ ሲናገሩ ታይተዋል፡፡ አንዱ ሌላው የሚያደርገውን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ጥያቄ ለማንሳት እንዲመቻቸው በትኩረት ነበር የሚመለከቱት፡፡

 

የግብፁ ሚኒስትር የኢትዮጵያ አቻቸውን በማሞካሸት እና የኢትዮጵያ መንግሥትን የማመስገን ተግባራቸውን በሁለቱም ቀናት ተይይዘውት ነበር የቆዩት፡፡ ከሁሉም ከተናገሩት ነገር አንድ አንድ ተሳታፊዎችና ታዛቢዎችን ያነጋገረው፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን በተከዜ እና በጣና በለስ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ እንኳን ደስ አለህ" ብለው፣ የተናገሩት ነበር አብዛኞቹ ተሳታፊዎች፣ ይህ ንግግር ከልብ የመነጨ ከመምሰሉ ይልቅ ዲፕሎማሲያዊ ንግግር እንደሚመስል ነበር የተናገሩት፡፡

 

አስራ ስምንተኛው የተፋሰሱ አገሮች ስብሰባ ሲጠናቀቅ፣ አቶ አስፋው የዓባይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊቀመንበርነቱን ከግብፁ / መሐመድ የተረከቡ ሲሆን፣ ሊቀመንበር ሆነው ለአንድ ዓመት እንደሚቆዩም ታውቋል፡፡ የኢኒሺኤቲቭ ዳይሬክተርነትን ግብጽ መጪው መስከረም ላይ ከኮንጎ እንደምትረከብም ታውቋል፡፡

 

በስብሰባው መቋጫ ላይም አንድ ልዩ ስብሰባ በቅርቡ እንደሚደረግና የተነሱትን ሕጋዊ አንደምታዎች እንደሚወያዩባቸው የሚኒስትሮቹ ምክር ቤት አስታውቋል፡፡

ሪፖርተር

 

Last Updated on Friday, 02 July 2010 06:57
 

Add your comment

Your name:
Subject:
Comment: