RedBlueDark SmallMediumLarge NarrowWideFluid
የቻይናው ሲአርቢሲ በክፍያ ምክንያት ሥራ ሊያቆም መሆኑን አስታወቀ PDF Print E-mail
Written by solomon   
Monday, 28 June 2010 16:00


በመንገድና በድልድይ ግንባታ የሚታወቀው የቻይናው ኩባንያ (ሲአርቢሲ)  ገንብቶ ለጨረሳቸውም ሆነ ወደ ፊት ለሚገነባቸው መንገዶች ክፍያ ስላልተፈጸመለት፣ ከሐምሌ 15 ቀን 2002 .. ጀምሮ ሥራ እንደሚያቆም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጻፈው ደብዳቤ አስጠነቀቀ፡፡2003 በጀት ዓመት ከሚጸድቀውና በሐምሌ ወር ከሚሰበሰበው ገቢ ክፍያውን ለመፈጸም በካቢኔ መወሰኑን፣ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የካቢኔው አባል ለሪፖርተር አሳውቀዋል፡፡

 


አስተዳደሩ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ቀለበት መንገድን ጨምሮ በርካታ የውስጥ ለውስጥና ሠፋፊ መንገዶችን በመሥራት ላይ የሚገኘው ሲአርቢሲ፣ ሠርቶ ያጠናቀቃቸውና ተመርቀው አገልግሎት መስጠት የጀመሩትን መንገዶች ክፍያን ጨምሮ፣ 200 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲከፈለው አስተዳደሩን በደብዳቤ መጠየቁን አንድ የኩባንያው ኃላፊ አስረድተዋል፡፡

 

ኩባንያው በሦስት ቁጥር ማዞርያ፣ በፑሽኪን አደባባይ፣ በመገናኛ፣ በቀበናና በሌሎችም አካባቢዎች ያሉ መንገዶችን ቢያጠናቅቅም፣ አስተዳደሩ ባጋጠመው የበጀት እጥረት ምክንያት ክፍያውን ሊፈጽምለት ባለመቻሉ ደብዳቤ ለመጻፍ መገደዱን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

 

ሲአርቢሲ መንገዶችን ለመገንባት ከአስተዳደሩ ጋር ሲፈራረም መንገዱ የሚፈጀውን የግንባታ ወጪ 20 በመቶ ከተከፈለው በኋላ፣ ግንባታውን ደረጃ በደረጃ ሲጨርስና በአማካሪ መሐንዲስ ሲረጋገጥ ተጨማሪ ክፍያ እንደሚከፈለው ቢስማማም፣ አስተዳደሩ አጋጥሞኛል በሚለው የበጀት እጥረት ምክንያት እስካሁን ያልተከፈለው 200 ሚሊዮን ብር በላይ እንዳለውና በደብዳቤ መጠየቁን ኃላፊው አረጋግጠዋል፡፡

 

ኩባንያው ካለፉት ሁለት ሳምንታት ጀምሮ በርካታ ሠራተኞችን በሁለት ምክንያቶች መቀነሱን የገለጹት ኃላፊው፤ አንደኛው በተወሰኑ አካባቢዎች የሚሠራቸው ሥራዎችን በማጠናቀቁ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አስተዳደሩ ክፍያ ካልፈጸመለት መክፈል ስለማይችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

በኩባንያው የሥራ ኃላፊ በአቶ ዘየደ ተስፋዬ ፊርማ ከሥራ የተሰናበቱት ሠራተኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሥራ በማቆማቸው ግራ መጋባታቸውንና የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው እንደማያውቁ ተናግረው፣ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ በሚያዘው መሠረት የሞራል ካሣ ክፍያ፣ የአገልግሎትና የመሳሰሉትን ክፍያዎች ፈጽሞ እንዲያሰናብታቸው እየጠየቁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አባል የሆኑና ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ ኃላፊ እንደገለጹት፤ አስተዳደሩ አጋጠመው የተባለው የበጀት ችግር እውነት መሆኑንና አስተዳደሩም የኩባንያውን ጥያቄ መቀበሉን፤ 2003 .. በጀት ከሐምሌ ወር ጀምሮ ከሚሰበሰበው ገቢ ለኩባንያው በቅድሚያ እንዲከፈለው በካቢኔ መወሰኑን አስረድተዋል፡፡

 

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሚዩኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት የሥራ ሒደት ኃላፊዎች ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካልንም፡፡

 

ሪፖርተር

 

Last Updated on Monday, 28 June 2010 16:12
 

Add your comment

Your name:
Subject:
Comment: