| የአዲስ አበባን የውኃ ችግር ለመቅረፍ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይደረጋል |
|
|
|
| Written by solomon | |||
| Monday, 28 June 2010 15:52 | |||
|
የአዲስ አበባ ከተማን የመጠጥ ውኃ ችግር ለመቅረፍ ለሚያስችለው ፕሮጀክት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ሊደረግ ዕቅድ ተይዟል፡፡ ባለፈው ሚያዝያ ወር በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ የተቋቋመው የግዢ አገልግሎት መሥርያ ቤት፣ የከተማዋን የመጠጥ ውኃ ችግርን ለማቃለል 40 ጥልቅ ጉድጓዶችን መቆፈር የሚያስችል ዓለም አቀፍ ጨረታ ሊያወጣ ነው፡፡ መሥርያ ቤቱ አዲስ እንደመሆኑ ይህ የሚያወጣው የመጀመርያው ጨረታ ይሆናል፡፡
በሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ የሚወጣውን ይህንን ዓለም አቀፍ ጨረታ የደቡብ አፍሪካ፣ የጣሊያን እና የእንግሊዝ ኩባንያዎች ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳደራቸውን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የከተማው ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ፣ አቶ መኩርያ ኃይሌ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የሚቆፈሩት ጉድጓዶች ጥልቀታቸው ከ500 ሜትር በላይ ሲሆን፣ እንዳስፈላጊነቱ እስከ 1000 ሜትር ድረስ ቁፋሮ እንደሚካሄድ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ቁፋሮው የሚካሔደው በከተማው ዳርቻ እና በተለይም ከተማውን በሚያዋስኑት የኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች ነው፡፡ ከአካባቢዎቹ መካከል አቃቂ፣ መልካ ቁንጥሬ፣ ሰበታ፣ ለገዳዲ እና አያት ይገኙበታል፡፡
የሚቆፈሩት ጥልቅ ጉድጓዶች በአንድ ሰከንድ ከመቶ ሊትር በላይ ውኃ ይገኝባቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በእስካሁኑ ሒደት ለከተማው የመጠጥ ውኃ ከሚገኝባቸው ከ70 በላይ ጉድጓዶች ውስጥ ከ500 ሜትር በላይ ጥልቀት ያላቸው ሁለት ጉድጓዶች ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት የተቆፈሩት በርካታ ጉድጓዶች ጥልቀታቸው ከ200 ሜትር በታች ሲሆን፣ በሰከንድ ውኃ የመስጠት አቅማቸው ከ15 ሊትር በታች በመሆኑ ነው የከተማው አስተዳደር ጥልቅ ጉድጓዶች ላይ ትኩረቱን ያደረገው፡፡ በውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ ላይ የተሠማሩ አገር ውስጥ ያሉ ኩባንያዎች ከ200 ሜትር በታች ብቻ የመቆፈር አቅም ያላቸው በመሆኑ ነው የግዥ አገልግሎቱ ዓለም አቀፍ ጨረታ እንዲያወጣ የተወሰነው፡፡ በአቶ ኩማ ደመቅሳ የሚመራው የከተማ አስተዳደር ሥልጣን ሲረከብ፣ የከተማው የውኃ ሽፋን 52 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ሥልጣን በተረከበ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ አስተዳደሩ የገፈርሳን ግድብ አቅም በማሳደግ እና ብዛት ያላቸውን ጉድጓዶች በመቆፈር ሽፋኑን ወደ 73 በመቶ አድርሶታል፡፡
"የ27 በመቶ ክፍተት አለብን፡፡ ይህንንም ክፍተት በዚህ ፕሮጀክት እንሸፍነዋለን፤" ሲሉ አቶ መኩርያ ይገልጻሉ፡፡ ጥልቅ ጉድጓዶቹ እንዲቆፈሩ የሚያስችለውን የመጀመርያ ጥናት ያካሔደው የውኃ ሀብት ልማት ሚኒስቴር ሲሆን፣ የሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ይህንን ጥናት ያካሔደው ጉድጓዶቹ በሚቆፈሩባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ገበሬዎች የመጠጥ ውኃ እንዲያገኙና በመስኖ የግብርና ሥራ እንዲካሒዱ ለማስቻል ነበር፡፡
ይህ ጥናት የከተማው አስተዳደር በዘላቂነት የከተማውን የመጠጥ ውኃ ችግር ለመፍታት አቅዶ የነበረውን የሲቢሉና የገርቢ ወንዞች ግድብ ፕሮጀክትን ችላ እንዲል እና ጉድጓዶቹ ላይ ትኩረቱን እንዲያደርግ አስችሎታል፡፡
"ምክንያቱም የግድቦቹ ጥናት ሲካሔድ አዲስ አበባ ከጉድጓድ በሚወጣ የመጠጥ ውኃ ችግሯን ትቅረፍ፣ አትቅረፍ አይታወቅም ነበርና ነው፤" ሲሉ ከተማው ትኩረቱን የጉድጓድ ቁፋሮ ላይ ያደረገበትን ምክንያት አቶ መኩርያ ይገልጻሉ፡፡
የመንግሥትን ትላልቅ ግዥዎችንና ሁሉም መንግሥታዊ መሥርያ ቤቶች በአንድነት የሚፈልጓቸውን ቁሳቁሶች ግዥ እንዲፈጽም የተቋቋመው የግዥ አገልግሎት መሥርያ ቤት፣ የሚያወጣውን የቁፋሮ ጨረታ የሚያሸንፉ ኩባንያዎች ከአቃቂው በስተቀር የሙከራ ቁፋሮ አድርገው ወደ ዋና ሥራቸው ይገባሉ፡፡
የአቃቂ አካባቢ ቀደም ሲል የተሞከረና በቂ ውኃ እንዳለው በተግባር ስለታየ ነው ሙከራ የማያስፈልገው ሲሉ አቶ መኩርያ አስረድተዋል፡፡
|
|||
| Last Updated on Monday, 28 June 2010 16:00 |
Add your comment
ADD
Comments, category: "amharic"
- የአዲስ ነገር ጋዜጣ አዘጋጆች ሕትመቱን አቋርጠው ተሰወሩ (4)
- እኛ ካላሸነፍን ምርጫው መጭበርበሩ ይታወቃል ሲሉ የአንድነት አመራሮች አስታወቁ (2)
- አቶ ስዬ አብርሃ መንታ መንገድ ላይ መቆማቸው ታወቀ (1)
- ከአፄው ስርዓት ጋር የሚመሳሰል የምርጫ ቅስቀሳ በተምቤን ተጀመረ (1)
- ኢትዮጵያ ግብረ-ሰዶም ባለመፍቀዷና ግልገል ጊቤን በማልማቷ ሁማን ራይትስ ዎች ከሰሰ፤ አቶ ገብሩ አስራትና አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በምንጭነት ተጠቅሰዋል (1)
- የኢ/ጉ/ገ/ ባለሥልጣን 6 ህገ ወጥ ነጋዴዎች ወደ ህግ ማቅረቡን አስታወቀ (1)











